በፋርማሲ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የሕንድ ኩባንያዎች ተደራሽነታቸውን በሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በፋርማሲ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ የሕንድ ኩባንያዎች ተደራሽነታቸውን በሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡
በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደው ውይይት፥ በኢትዮጵያ በፋርማሲው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የሕንድ ኩባንያዎች ተወካዮች በዘርፉ ተደራሽነታቸውን በሚያሳድጉባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡
ሕንዳውያን ባለሀብቶች መዋዕለ-ንዋያቸውን በዘርፉ ላይ እንዲያፈስሱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ነው የተወያዩት፡፡
ከፈረንጆቹ መጋቢት 3 እስከ 5 ድረስ ኢትዮ-ሜዲካል ኮንግረስ እና ዐውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅና 50 የሚሆኑ የሕንድ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በኢትዮጵያ ከሕንድ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃው አመላክቷል፡፡
ተጋባዥ እንግዶችም ከሕንድ ኩባንያዎች እና ባለሀብቶች ጋር ተገናኝተው የሚወያዩበት መድረክ እንደሚፈጠርላቸው ነው የተመለከተው፡፡
ከኮንግረሱ እና ከዐውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን የሕንድ ተወካዮች እና የመድሓኒት አምራቾች ፣ አስመጪዎች እና ጠቅላላ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚወያዩበት መድረክ እንደሚፈጠርም ነው ኤምባሲው ያሳወቀው፡፡