Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ ድጋፍ የሚተገበረው ”ከፍታ” የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ የሚተገበረው ” ከፍታ” የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆነ፡፡
ከፍታ ፕሮጀክት የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ሲሆን÷ 60 ሚሊየን ዶላር በጀት የተመደበለትና በ5 ዓመታት የሚጠናቀቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ 2 ሚሊየን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በ18 የሀገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶችን ያሳትፋል ነው የተባለው፡፡
በከፍታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ÷ የሀገሪቱ 70 በመቶ ያህል የኅብረተሰብ ክፍል ወጣት በመሆኑ ንቁ የሆነ ፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ቢሆንም÷ በመንግስት ብቻ የሚደረግ ጥረት በቂ ባለመሆኑ የሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ የሚተገበረው ከፍታ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት የወጣቶችን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ እምነት እንደተጣለበት እና ለዚህም መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱም ውሳኔ ሰጪነትን ያዳበሩ፣ ስራ ፈጣሪ፣ተሰጦአቸውን ያጎለበቱና በውይይት የሚያምኑ ወጣቶችን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የተዘጋጀውን ከፍታ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት ለማስጀመር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
አምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ ጤና ተኮር ስራዎችን በሴቶችና በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በዘቢብ ተክላይ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.