Fana: At a Speed of Life!

የጦር መሳርያ መነጽሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ሊያስገባ ሲሞክር የተያዘው ተከሳሽ በገንዘብና በእስራት ተቀጣ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለማለምና ለማነጣጠር  የሚያገለግሉ  የጦር መሳርያ መነጽሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ሊያስገባ ሲሞክር የተያዘው ተከሳሽ በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና  በ1 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወሰነበት።

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረደው÷ አንድሪስ ሙሀመድ የተባለው ተከሳሽ  ፍቃድ ሳይኖረው ህዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 3:10  ሲሆን÷ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዱባይ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ  በተደረገው ፍተሻበቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በዕለቱ ይዞት በመጣው ሻንጣ ውስጥ በካርቶንና አልሙኒየም የተጠቀለሉ በተለያየ የጦር መሳርያዎች ላይ ተጠምዶ ለማለም እና ለማነጣጠር የሚያገለግል፤ ከፍተኛ ሀይል ያለው የተለያዩ ቀለማትን (ብርሃን) ብርሃን በሌንሱ ላይ በመቀያየር የሚሰራ፣ በቀላል የጦር መሳርያዎች ላይ ተጠምዶ በማነጣጠር ቀይ የነጥብ ምልክት በታለመለት ኢላማ ላይ በማሳረፍ ለተኳሽ ምልክት የሚሰጥ ማነጣጠሪያ መነጽሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ  ነው የተያዘው፡፡

ግለሰቡ በፈፀመው የጦር መሳርያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ዓ.ም አንቀፅ 4/1/ እና አንቀፅ 22/3/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ  የፀና ፍቃድ ሳይኖር የጦር መሳርያ መነጽር ወደ ሀገር ማስገባት ወንጀል መከሰሱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተከሳሽ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ÷ “ዐቃቤ ህግ የመሰረተብኝን ክስ ተረድቼዋለሁ  ነግር ግን በክሱ ላይ የተገለፀው የጦር መሳርያ መነጽር የእኔ ሳይሆን በዱባይ ሀገር የሚገኘው ጓደኛዬ ለቤተሰቦቼ አድርስልኝ ብሎ የተለያዩ የእጅ ባትሪዎችን አንደሰጠኝ አንጅ  ከባትሪዎቹ ጋር የጦር መሳርያ መነጽሮች  ጨምሮ እንደሰጠኝ አላውቅም ነበር  ”  ሲል ቃሉን የሰጠ ቢሆንም÷ ጥፋተኛ መሆኑን ያልተቀበለ በመሆኑ ጥፋተኛ መሆኑን እንዳላመነ ተቆጥሮ  ዐቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን አቅርቦ እንዲያስደምጥ በችሎቱ ተገልጾለታል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ÷ ተከሳሽ ጥፋተኛ ስለመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳሉ ያላቸውን ዝርዝር የሰው፣ የሰነድና የኢግዚቢት ማስረጃዎች አቅርቦ ያሰማ ሲሆን÷ በቀረበው ክስ እና ማስረጃ ተከሳሽ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች አቅርቦ  እንዲያስተባብል ፍርድ ቤቱ ብይን ቢሰጥም ተከሳሹ ማስተባበል ያልቻለ በመሆኑ  የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል::

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል ሲል ተከሳሽ በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና በ1 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.