በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ከ2 ሺህ 600 በላይ ካርቶን ዘይት ተከማችቶ ተገኘ
የካቲት 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ሲዳሞ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ህንፃ ምድር ቤት ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው የምግብ ዘይቶቹ ተከማችተው የተገኙት።
ግለሰቦቹ የተሰጣቸውን የንግድ ፈቃድ ሽፋን በማድረግና አሁን ያለውን የዘይት አቅርቦት እጥረት ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም አከማችተው እንደተገኙ ተገልጿል፡፡
ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በ8 ነጋዴዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ባለ 3 ሊትር 441 ካርቶን፣ ባለ 5 ሊትር 129 ካርቶን፣ ባለ 1 ሊትር 65 ካርቶን፣ ባለ 5 እና 3 ሊትር 2 ሺህ 100 ካርቶን በአጠቃላይ ከ2 ሺህ 600 በላይ ካርቶን የምግብ ዘይት ሊያዝ ችሏል፡፡
ይህም ለህብረተሰቡ በወቅቱ መድረስ የነበረበት ቢሆንም ነጋዴዎቹ በአንድ ህንፃ ምድር ቤት ውስጥ አከማችተው የተገኙ በመሆናቸው መጋዝኖቹም እንዲታሸጉ መደረጉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት÷ አንዳንድ ነጋዴዎች ህጋዊ የንግድ ፈቃድን እንደ ሽፋን በመጠቀም ህገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ በመኖራቸው ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።