Fana: At a Speed of Life!

በሽብርተኛው ህወሓት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የመርሳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው እና ወራሪው ህወሓት ከፍተኛ ጉዳትና ዝርፊያ ተፈጽሞበት የነበረው የመርሳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
 
በ2012 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የነበረውና በርካታ አዳዲስና ውድ መሳሪያዎች ተተክለውለት የነበረው የመርሳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህወሓት ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ ተፈጽሞበት እንደነበር ተወስቷል፡፡
 
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ተስፋዬ÷ አሸባሪው ቡድን በሆስፒታሉ ላይ 119 ሚሊየን ብር የሚገመት ውድመት ማድረሱንም ነው የገለጹት፡፡
 
400 ሺህ ያህል ህብረተሰብ የሚያገለግለው ይህ ሆስፒታል ÷ ውድመት ከተፈጸመበት በኋላ ከሀዋሳ ቲቺንግ ሆስፒታ፣ ከሸበል በረንታ ሆስፒታልና ከወፋ ፋውንዴሽን ÷ የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን በድጋፍ እንዳገኘ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል ፡፡
 
በተጨማሪም ሆስፒታሉ ሳማሪታን ፐርስ ከተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ከፍተኛ የህክምና መሳሪያዎችን ማግኘቱን አቶ አድማሱ ተናግረዋል ፡፡
 
በአሁኑ ሰዓት ሆስፒታሉ በድጋፍ ያገኛቸው መሳሪያዎች የቀዶ ህክምና እንዲሁም የጽኑ ህሙማን አገልግሎት መጀመር የሚያስችሉ በመሆናቸው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያስችላዋል ብለዋል።
 
ሆስፒታሉ የሚደግፋቸው 7 ጤና ጣቢያዎች እና 43 ጤና ኬላዎችም ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው ቀጣይ ድጋፍ በማድረግ አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ ማስጀመር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
 
ለዚህም መንግስት፣ መላው ማህበረሰብና አጋር ድርጅቶች እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በአንድነት ናሁሰናይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.