የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአፋር ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ተመለከቱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተፈናቅለው በኮሪ ወረዳ “ጉያህ” መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ ተመለከቱ።
የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተወካይ አቶ ማሄ አሊ ለድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን÷ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በክልሉ በ21 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል ብለዋል።
“ከተጎጂዎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉም” ነው ያሉት።
ከተፈናቀሉት ውስጥ በቅርቡ በቂልበቲ-ረሱ ዞን በሽብር ቡድኑ በአምስት ወረዳዎች በተፈጸመ ወረራ ተፈናቅለው በ14 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 294 ሺህ ሰዎች ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም አብራርተዋል።
በኩሪ ወረዳ የጉያህ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን ጨምሮ ከአብአላ፣ በራህሌና ኩነባ ወረዳዎች የተፈናቀሉ አባወራዎች የዚሁ አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግስት ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ለተፈናቃዮች ምግብና አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲሁም መጠለያዎችን እያቀረበ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አኳያ ብዙ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
ተፈናቃዮች ከችግሩ ስፋት አኳያ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!