Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ “ከፈተና ወደ ልዕልና!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የጉባኤው የመክፈቻ ስነ ስርዓት የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የውጭ ሀገራት ወዳጅ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ፓርቲው አስታውቋል።
ጉባኤውን አስመልክቶ የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ፥ የብልጽግና አንደኛ ጉባኤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፓርቲው በሁሉም መስክ የተጎናጸፋቸውን ድሎች እንደሚገመግም ተናግረዋል።
ፓርቲው የገጠሙትን ችግሮች እና ተግዳሮቶች በጥልቀት ገምግሞ ለማረም ታሪካዊ ውሳኔ ያሳልፋልም ነው ያሉት።
ጉባኤው በጸጥታ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክርም ገልጸዋል።
በዚህም ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያመጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ነው ያስታወቁት።
በጉባኤው 1 ሺህ 600 የፓርቲው አባላት በድምፅ የተሳተፉ ሲሆን፥ 400 ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ እንግዶች ያለ ድምፅ እየተሳተፉ ነው ።
ጉባኤው የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት የሚጎናጸፉበት፣ ፓርቲው በአደረጃጀት እና አሰራር ራሱን የሚያጠናክርበት እንዲሁም ፓርቲውን ሊያሻግሩ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጠንካራ የፓርቲ አመራሮች የሚመረጡበትም ይሆናል ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ የቅድመ ጉባኤ መድረክ በትናንትናው ዕለት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በማጠቃለያ መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን ከዚህ ቀደም በሀገራችን የሰራነውን የማፍረስ፣ አንድ ከሚያደርጉን ይልቅ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት እንዲሁም ገቢራዊነት መጓደልና ግለሰቦች ከሀገር በላይ የሆኑበት ሁኔታዎች ይስተዋሉ ነበር ብለዋል፡፡
ብልጽግና እነዚህን ችግሮች በሚፈታ መልኩ እየተጓዘ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው÷ ከስርዓትና ከተልዕኮ አፈፃፀም ጋር የሚያያዙ ችግሮችን መፍትሄ በመስጠት እንዲሁም ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የፓርቲውን የአጭር ጊዜ እቅዶችና የረጅም ጊዜ ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በዓልአዛር ታደለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.