Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት ከ9 ሺህ 500 በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት በጋምቤላ ክልል ከ9 ሺህ 500 በላይ የላሬና የጂካዎ ወረዳ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግስት እንደገለጸው፥ በግጭቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ፥ በሰድስት ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ታጣቂዎቹ የኢትዮጵያን እና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን ዘርፈው ወስደዋል።

የተፈናቀሉት በኑዌር ዞን በላሬና በጂካዎ ወረዳዎች ሥር የሚገኙ የአራት ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸው ተመልክቷል።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ፥ በደቡብ ሱዳን የኤስ ፒ ኤል ኤም-ኤልኦ ወታደሮችና በደቡብ ሱዳን መንግስት መካከል ሰሞኑን ግጭት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

የጋምቤላ ክልልና ደቡብ ሱዳን ሰፊ ድንበር የሚጋሩ ከመሆናቸዉ ጋር ተያይዞ በድንበር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ድንበር አቋርጠው የገቡ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል።

በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ተኩስ በመከፈቱ ከ 9 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑ አቶ ኡገቱ ገልጸዋል።

የተዘረፉ እቃዎችን ለማስመለስ መንግስት የጸጥታ ሀይሉን አሰማርቶ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ፥ ታጣቂዎች ድንበር አልፈው እንዳይገቡም ተገቢው ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከተፈናቃዮቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ለተጎጂዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማድረግ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ንግግር መጀመሩን ነው የገለጹት።

በግጭቱ ምክንያት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ላሬና ጂካዎ ግዛቶች የገቡ ደቡብ ሱዳናዎያን መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ኡገቱ፥ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል፡፡

በላሬ ወረዳ የብሊምኩን ቀበሌ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸዉ ለመመለስ መንግስት አስፈላጊውን እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.