የቢሾፍቱ ከተማ በምዕራብ እና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር በምዕራብ እና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ እህል እርዳታ አድርጓል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ መኮንንን ባይሳ እንደገለጹት÷ አስተዳደሩ ለወገን ደራሽ ወገን ነው! በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን ድጋፍ ነው በድርቅ ለተጎዱ ገኖች ያደረሰው፡፡
ድጋፉ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከጎናቸው መሆናችን ለማሳየት የተደረገ ነው ብለዋል ሃላፊው።
በቀጣይም ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ የአበባ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ዩኒቨርስቲን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ 7ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በነበረው የጦርነት የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው ተብሏል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች 10 ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በመሆን የወሎ ዩኒቨርስቲ፣ የወልድያ ዩኒቨርሺቲና የመቅደላ ዩኒቨርስቲን ለመደገፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተናግረዋል፡፡