ብሪታኒያ ከ370 በላይ ተጨማሪ ሩስያውያን ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች
አዲስ አበባ፣መጋቢት 6፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታኒያ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ቅርበት አላቸው ባለቻቸው ከ370 በላይ ተጨማሪ የሩስያ ዜጎች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች፡፡
ብሪታኒያ በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አጋሮች ናቸው ባለቻቸው የሩስያ ዜጎች ላይ ማዕቀቧን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፥ የአልፋ ባንክ መስራች ሚካሂል ፍሪድማን፣ የሌተር ኦን መስራች ፒተር አቨን እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን ጨምሮ ከ370 በላይ ሩስያውያን ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ፣ የክሬምሊን ፕሬስ ሴክሬታሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ቀደም ሲል በዩናይትድ ኪንግደም ማዕቀብ በተጣለባቸው የቅርብ ግለሰቦች ሲሆኑ ባጠቃላይ ማዕቀብ የተጣለባቸው ዜጎች ቁጥር ከ 1 ሺህ በላይ መድረሱን ብሎምበርግ አስነብቧል፡፡
በሌላ በኩል ለዩክሬን የድጋፍ ማዕቀፍ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር ለመነጋገር የሦስት የምሥራቅ አውሮፓ አገራት መሪዎች የሰዓት እላፊ ወደተጣለባት ዋና ከተማዋ ኪዬቭ በባቡር እያመሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የፖላንድ፥ ቼክ እና ስሎቫኪያ መሪዎች ወደ ኪዬቭ ያመሩት ለዩክሬን ሉዓላዊነትና ነፃነት ያለንን ጽኑ ድጋፍ በመላው አውሮፓ ህብረት ስም ለመግለጽ ነው ሲሉ የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትር ፊያላ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!