Fana: At a Speed of Life!

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ግብ እንዲሳካ አካታች መንገዶችን መከተል እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽነሮች የተሾሙለት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ግቡን ያሳካ ዘንድ ከወዲሁ አካታች መንገዶችን ሊከተል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ማርሸት ታደሰ÷ አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ምሁራን፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፥ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች፥ ሲቪል ማኅበራትና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጎ አሻራቸውን ሊያሳርፉ ይገባል ይላሉ፡፡
የሕግ ባለሙያው አምሃ መኮንን በበኩላቸው÷ የፖለቲካው አለመረጋጋት የፈጠረውን ቀውስ ለማረቅ ብሎም በአገራዊ ምክክሩ አስተማማጥ ውጤት ለማግኘት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አካታችነትን መሰረት ያደረጉ በሰከነ መንገድ ውይይቶችን በማካሄድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል።
የሕግ ምሁራኑ እንደሚያስረዱት አንኳር ለሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት የሽግግር ፍትህን ለማስፈን የሚያስችሉ አሰራሮችን በምክክር ሂደቱ መመልከት እንደሚገባም ጠቁመዋል ።
ኮሚሽኑ በተቀመጠለት ዓላማ መሰረት ጠንካራና ተአማኒ መሆኑን የሚያረጋግጡ ስራዎችን በነፃነት እንዲያከናውን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም የህግ ምሁራኑ አብራርተዋል ።
መገናኛ ብዙኃንም ከመሰረታዊው ጉዳይ ጀምሮ የምክክር ሥራው ሂደቶች በግልጽነት፥ በተዓማኒነትና በምክንያታዊነት እዲከናወኑ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ነው የጠቆሙት።
በአገራዊ ምክክሩ ዜጎችም ቀናኢና ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው የሕግ ምሁራኑ ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክሩ ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን መቻቻል እና መከባበርን መሰረት ያደረጉ፥ አካታችነትን ያካተቱ፥ ግልፅነትን የተላበሱ ውይይቶች ማካሄድ አለባቸው፥ ለዚያም ከወዲሁ በቂ ዝግጅት መደረግ አለበት ብለዋል ምሁራኑ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ውስጥ፥ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፥ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላደል መፍጠር፤ ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት ፅኑ መሠረት መጣል የሚሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።
በአወል አበራ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.