የማንነት፣ አስተዳደር ወሰን እና ግጭት አፈታት አቤቱታ አቀባበል፣ አያያዝና ምላሽ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት የአስተባባሪና የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት በማንነት፣ አስተዳደር ወሰን እና የግጭት አፈታት አቤቱታ አቀባበል፣ አያያዝና ምላሽ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ላይ መክረዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ ምክር ቤቱ አስጠንቶ ተግባራዊ ያደረገውን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ በተወካዮች ምክር ቤት የወጡትን አዋጆች ተከትሎ ልዩ ልዩ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በማጽደቅና የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶችን ለይቶ በመሙላት ሥራዎችን በውጤታማነት መፈጸም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት የአቤቱታ አቀባበል፣ አያያዝ እና ምላሽ አሰጣጥ መመሪያ ባለመኖሩ ምክንያት የታዩትን ክፍተቶች በመሙላት ሥርዓቱን ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ለዚህም አቤቱታ አቅራቤዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተግባራቸውን ስርዓት ባለው መልኩ እንዲያከናውኑ የሚያስችል የአቤቱታ አቀባበል፣ አፈታትና ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን በማብራራት ዝርዝር ረቂቅ መመሪያውን አቶ ጴጥሮስ አቅርበዋል።
የአስተባባሪውና የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላቱ በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ሊካተቱ የሚገባቸውን ግብዓቶች እንዲካተቱ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከፌደሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አባላቱ ምክር ቤቱ አስጠንቶ ተግባራዊ ያደረገውን ሪፎርም መሠረት በማረግ የምክር ቤቱን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!