በጌዴኦ ዞን በአይነስውር ተገልጋይ ላይ በደል ያደረሱ የጤና ባለሙያዎች ከስራ ታገዱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ በሚገኘው በጪጩ ጤና ጣቢያ ውስጥ ወላድ በሆኑ አይነስውር ተገልጋይ ላይ በደል ያደረሱ የጤና ባለሙያዎች ከስራ ታገዱ።
በዞኑ ጤና ጣቢያ ውስጥ አይነስውር በሆኑ ወላድ እናት ላይ በታየው የአገልግሎት አሰጣጥ እንግልት ምክንያት በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር።
በዲላ ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው በጪጩ ጤና ጣቢያ የተገላገሉት ወይዘሮ ስምረት ጥላሁን አይነስውር ሲሆኑ÷ በተቋሙ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሊሻሻሉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
“ነፍሰጡር እንደመሆኔ ከምጥ ጊዜ ጀምሮ እስከምወልድበት ድረስ ማየት እንኳን ባልችልም በተቋሙ የነበሩት ሰራተኞች እያስተናገዱኝ እንደነበር ይሰማኝ ነበር” ያሉት ወይዘሮ ስምረት÷ ህጻኑን በሠላም መገላገላቸውን ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ከወሊድ በኋላ ወደ ማቆያ ክፍል በማለት የተወሰድኩበትን ቦታ ማየት ባልችልም ከእናቴ ያገኘሁት መረጃ ቅር አሰኝቶኛል ብለዋል፡፡
በወቅቱ አብረዋቸው የነበሩት የወይዘሮ ስምረት ጥላሁን ወላጅ እናት ወይዘሮ ብርቅነሽ ብሬ በበኩላቸው÷ የተከሰተው ክስተት እና ልጃቸው እንድታርፍ የተደረገበት ቦታ ተገቢ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።
ተገልገይዋ ላይ በተፈጠረው ችግር የጤና ጣቢያ ሃላፊውን ጨምሮ 3 ባለሙያዎች ላይ የስራ እገዳው መጣሉ ተገልጿል።
የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ኩኡ እንደገለጹት÷ ድርጊቱን በፈጸሙት አካላት ላይ በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ ይገኛል።
ክስተቱ አሳዛኝ መሆኑን የገለፁት የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ተገኝ ታደሰ በበኩላቸው÷ በጊዜው የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ለወይዘሮ ስምረት ጥላሁን ተገቢውን ክትትል ባለማድረጋቸው ለተፈጠረው ችግር መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ስለድርጊቱ መላውን የጌዴኦንና የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ ማስታወቁን ከጌዴኦ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!