የአፋር ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ተጨማሪ በጀት እና ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን አንደኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ከ253 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
የምክር ቤቱ ጉባኤ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ ባቀረቡት ተጨማሪ በጀቱ ላይ መክሯል።
ተጨማሪ በጀቱ ከክልሉ የውስጥ ገቢ አርዕስቶች እንደሚሸፈን ያመለከቱት ሃላፊው÷ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሠላም እሴት ግንባታ ስራዎች እንደሚውል አብራርተዋል።
የቀረበው ከ253 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል ምክር ቤቱ መርምሮ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም ወይዘሮ ፋጡማ አደም የህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና ወይዘሮ ጀሚላ ቡርኡሌ ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳይ ቋሚ ኮሜቴ አባል ሆነው እንዲሰሩ በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አስያ ከማል አቅራቢነት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ በሠመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቋል።