በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ድህረ-ጉባኤ የሕዝብ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባሕር ዳር እና ጎንደር የብልፅግና ፓርቲ ድኅረ-ጉባኤ የሕዝብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በባሕር ዳር እየተካሄደ ባለው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቋሞች ላይ በሚመክረው ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃ ከፋለን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማም በመድረኩ ተገኝተዋል።
የጉባኤው አላማ የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች እንዴት ሊፈታው እቅድ ይዟል በሚለው ላይ መወያየት መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ ባለፈም ከጉባኤ በኋላ ከህዝብ ጋር ተወያይቶ በጸጥታ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና መሰል ዘርፎች መወያየት መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሉባት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አንደኛው ችግር የፖለቲካ ዜሮ ድምር አዙሪት መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ወቅትም ብልጽግና ፓርቲ ካለፉት ፓርቲዎች የሚለይባቸውን የህብረ ብሄራዊነት እሴቶች አንስተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን÷ እንደሀገር ባለፉት ጊዜያት ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።
በዚህም የዜሮ ድምር ፖለቲካ አዙሪት አንዱ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የአግላይነት፣ የእኩል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ባለፉት ጊዜያት በነበረው የፓርቲው ጉዞ በአንድነት ያሳካቸው የልማት እና የብልጽግና መልኮች እንዳሉ ሁሉ ፈተናዎችም እንዳሉበት ነው የተናገሩት፡፡
አማራ፣ ቅማንት፣ አርጎባ፣ አማራ እና ኦሮሞ ወዘተ በሚል የልዩነት ሰበብ መገፋፋታችን ትልቅ በሽታ ሆኖብናልም ነው ያሉት፡፡
ዶክተር ይልቃል አክለውም ብልጽግናን ለማረጋገጥ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ጠቅሰው፥ ለአብነትም የባህል ሽግግር ማድረግ እና የስራ ባህልን አንስተዋል።
የከተማ እና የገጠር ግብርናን ማፋጠን ይገባል በዚህ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን መፍታት አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በዚህ ውይይት ከውስጥ እና ከውጭ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መፍታት ይገባል ብለዋል።
የጉባኤው አንዱ አላማ መግባባት መሆኑን አንስተው፥ ጸጥታን በተመለከተም የሕግ የበላይነት ችግሮች እንዳሉ አመላክተዋል፡፡፡
በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ የፈተናወች መብዛት ከብልፅግና ጉዟችን አይደናቀፍም በሚል መፈክር እያካሄደ በሚገኘው ውይይት÷ የኢፌዴሪ የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ አለምን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል።
ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ጎንደር ከተማ የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች በውይይቱ እየተሳተፉ ነው፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት አገራችን ወደከፍታ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
አንደኛ ጉባኤ ባካሄድን ማግስት በቀጥታ ከሕዝብ ጋር በመምከር የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ይህን አይነት ውይይት ማድረጉም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፓርቲው ውይይቱን ከሕዝቡ ጋር እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የብልፅግና ፓርቲ ድህረ ጉባኤ የህዝብ ውይይት መድረክ በደብረብርሃን ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በመድረኩ የብልፅግና ፖርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር አብዱ ሁሴን፣ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ያሲን፣ የአማራ ክልል ገጠር መሬት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እና የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ተገኝተዋል፡፡
በለይኩን ዓለም፣ ኤልያስ አንሙት እና አበበ የሸዋልዑል
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!