የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቋሞች ላይ የሚመክር የህዝብ ውይይት በአዳማ እና ጅማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቋሞች ላይ የሚመክር የህዝብ ውይይት በአዳማ እና ጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በአዳማ ከተማ እየተደረገ በሚገኘው መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በጅማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ደግሞ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እና የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የመድረኩ አላማ የፓርቲው ጉባኤ ውሳኔዎችን ህዝቡ በዝርዝር እንዲያውቅ ማድረግ፣ ውሳኔዎቹ ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆናቸውን የህዝብ አስተያየት ማከልና ለውሳኔው መሳካት ህዝቡ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የሃገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሙስና፣ ሌብነትና የኑሮ ውድነት ትልቅ ተግዳሮቶች መሆናቸውንና በእነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱል ሃኪም ሙሉ፥ አግላይነትና ፅንፈኝነት፣መገፋት ወደ ብልፅግና በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ፈተናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጅማ እየተካሄደ ባለው ውይይት የከተማው ነዋሪዎች “መንግስት በራሱ መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው የህዝቡን የመከራ ጊዜ የሚያራዝሙ ሙሰኛ አመራሮችን ለይቶ እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በፀጥታ ተቋማት ውስጥ የተዘረጋው ሌብነት ሰላም እንዳይረጋገጥና ህብረተሰቡ በሰላም እጦት እንዲሰቃይ ምክንያት መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
የኑሮ ውድነት መኖር ከማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ነዋሪዎቹ፥ በነጋዴውና በአንዳንድ አመራሮች መሃል የተዘረጋው የጥቅም ሰንሰለት ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም መንግስት ይህንና ሌሎች ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል።
በሙክታር ጠሃ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!