Fana: At a Speed of Life!

ክልሉን ከጦርነት ለማውጣት በፌደራልም በክልልም በኩል ሙሉ ፍላጎት አለ – ዶክተር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ከጦርነት ለማውጣት በፌደራልም በክልልም በኩል ሙሉ ፍላጎት መኖሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።
የብልፅግና ፓርቲ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተወከሉ ነዋሪዎች ጋር በባህር ዳር ከተማ የተወያየ ሲሆን፥ በውይይቱ ላይ ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ከእነዚህም መካከል “ለውጡ ሲመጣ በጣም ተደስተን ነበር፤ የአማራ ሕዝብ ደግፎ ነበር አሁን ላይ ግን ተሸርሽሯል፣ ከእስር የተፈቱ የአሸባሪው ህውሓት አባላት ጉዳይ የፈሰሰውን ደም ዋጋ ያሳጣ ነው፤ ከመቀሌ የመከላከያ ሰራዊቱ የወጣበት መንገድም አማራን ለጥቃት የዳረገ ነው” የሚሉ ይገኙበታል።
በተጨማሪም የ12ኛ ክፍል የአማራ ክልል ተማሪዎች 18 በመቶ ብቻ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣታቸው ቅሬታ መፍጠሩን በማንሳት አሰራሩ ድጋሜ እንዲፈተሽ ጠይቀዋል።
“የክልሉ አመራሮች ለክልላቸው በተቆርቋሪነት አይሰሩም” ያሉት ተሰብሳቢዎቹ፥ “ሸኔ ብቻውን አይደለም፤ ሀገር እያተራመሰ ያለው በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚደግፈው ስላለ ይሆናል” የሚል ሀሳብንም ተሳታፊዎቹ ሰንዝረዋል።
“ከአማራ ክልሉ ውጭ ለሚኖሩ አማራዎች ጥበቃ እንዲደረግ እንደዚሁም በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ የሰቆጣ ነዋሪዎች ትኩረት ይደረግ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለተነሱ ጥያቄዎች በመድረኩ መሪዎች በኩል መልስ ተሰጥቷል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይበልጣል ከፋለ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ ክልሉን ከጦርነት ለማውጣት በፌደራልም በክልልም በኩል ሙሉ ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው÷ ቅድሚያ መሳካት ያለባቸው ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከፋኖ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ዶክተር ይልቃል በሰጡት ምላሽ÷ “ፋኖ ትጥቅ አይፈታም፤ አይሳደድም፤ አይገፋም” ብለዋል። ነገርግን በአደረጃጀቱ ስም የሚሰራ ወንጀልን እና ህገወጥነትን በጋራ መከላከል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከ12ኛ ክፍል ውጤት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄም አጣሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፥ የሚመጣውን ውጤት አይተን አቋም እንይዛለን ብለዋል።
በኑሮ ውድነት ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ያሉት ዶክተር ይልቃል÷ የብልጽግና ፓርቲ ከሕጋዊ አሰራር ውጭ ገንዘብ ወስደዋል በተባሉት ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል። በዚህም በዚሁ ድርጊት የተሳተፉት ከፓርቲው እንዲታገዱ መደረጉን ተናግረው÷ ቀጣይ ማጣራቶችም ይደረጋሉ ብለዋል።
ከልማት ጋር ተያይዞ ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ማብራሪያ በልማት በኩል ኢንቨስትመንትን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው አሸባሪው ሸኔን በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ አሸባሪው ህወሃት በደቡብ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ከሸኔ ጋር በትብብር ለጥፋት ተሰልፈው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በለውጡ ሰሞን በትብብር ጥፋት መፈጸማቸውን ገልጸው፥ ከክልሉ ስፋት አንጻርም በተለይ በኬንያ ድንበር ከውጭ እየሰለጠኑ መግባታቸውን ነው ያብራሩት፡፡
ይህም ሆኖ በምዕራብ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሸኔን ለማጥፋት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ለአብነትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጸጥታ ኃይሉን በማጠናከርና አመራሩን በማጥራት በኩል ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ጥረት መካከል ነው የሰሜን ዕዝ የተጠቃው ያሉት አቶ ፈቃዱ÷ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሸኔ እና ህውሓት በጦርነቱ ወቅት ተናበው ይሰሩ እንደነበር ጠቁመው፥ በተለይ አዲስ አበባ ለመግባት ዕቅድ እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ ሸኔን ለማጥፋት ኦፕሬሽን መሠራቱን አብራርተው፥ አሁን በኦሮሚያ የተፈናቀሉ 8 ነጥብ 7 ሚሊየን ሕዝብ የምግብና ሌሎችም ድጋፎች እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል። 50 በመቶ ያህሉ በሸኔ ምክንያት እንደተፈናቀሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በሸኔ ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ሸኔ የሁሉም ጠላት በመሆኑ ቡድኑን ለማጥፋት ኦፕሬሽን መደረጉ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በምስራቅ ወለጋ 94 ሰዎች ከሸኔ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተው፥ በሆሮ ጉድሩም የተሻለ አመራር አለ፤ ይህን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
የተፈናቀሉትን ለመመለስ ኮሚቴ መዋቀሩን የገለጹት አቶ ፈቃዱ÷ የሁለቱን ሕዝብ የማግባባት፣ የማነጋገር እና የማስተሳሰር ስራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም አመራር የማጽዳቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት÷ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ በሰከነ መንፈስ በጋራ ያለፍነውና ያሳካነው ብዙ በመሆኑ ተደማምጠን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
በመንግሰት በኩልም የህዝብን ሃሳብ በመስማት በሰላምና በኢኮኖሚው ህዝብን በማስተባበር እና አንድነትን ለማጠናከር እንዲሰራ መክረዋል።
በለይኩን ዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.