ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሠራ ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአሸባሪው ሸኔ የተፈናቀሉ 692 ሺህ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡
አንድ የምክር ቤቱ አባል በህልውና ዘመቻ በመሰዋታቸው እና አንድ ሌላ አባል በህመም ህይወታቸው በማለፉ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነው ጉባዔው የተጀመረው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን መሰረተ ልማቶችን ቢያወድምም በሕዝብ ትብብር የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ወደ ልማት መገባቱን ተናግረዋል።
በአንጻሩ የተፈናቃይ ቁጥር መጨመር፣ የዋጋ ግሽበት፣ የሕግ ማስከበር ችግሮች፣ የማስፈጸም አቅም ድክመት፣ የአገልጋይነት ስሜት ማነስ ፈተና መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
የወደሙ ተቋማትን ለማቋቋም ለተባበሩ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለባለሃብቶች፣ ለዳያስፖራው እና እርዳታ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጥ እና ብልሹ አሠራሮች ላይም ብዙ መሠራት እንዳለበት ነው ያመላከቱት፡፡
በጉባኤው የ2ኛ መደበኛ ጉባኤ አጀንዳዎች ቀርበው የፀደቁ ሲሆን÷ የምክር ቤቱ መስራች እና 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ቀርቦ ጸድቋል። በዚህም ለሕግ፣ ፍትሕ አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ ወርቅነህ እንግዳው እንዲሁም ለግብርና አካባቢ ጥበቃና የውኃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑን ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
የ2014 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የተጠቃለለ የአስፈጻሚ አካላት የዕቅድ አፈጻጸም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ሪፖርት ቀርቧል።
በሪፖርቱም በህወሓት የተሰነዘረውን ወረራ ለመቀልበስ፣ የክልሉን የጸጥታ ኃይል ለማጠናከር እና በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የተሰሠሩ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህም ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአሸባሪው ሸኔ የተፈናቀሉ 692 ሺህ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም የክልሉን ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የፀጥታ መዋቅሩ የቅንጅት ሥራውን ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዜጎች ሠላምና ደኅንነት የፀጥታ አመራሩ ራሱን ማብቃትና የወንጀል መከላከል ተግባሩን ሊያጠናክር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
አክለውም አሸባሪው ህወሓት ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይል ማጠናከርና ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ በግብርና 4 ሚሊየን 391 ሺህ 276 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ የተገለጸ ሲሆን÷ በዚህም የዕቅዱን 96 ከመቶ መሸፈን መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ እስካሁን 4 ሚሊየን 192 ሺህ 94 ሄክታር መሬት ምርት በመሰብሰብ የዕቅዱን 93 ከመቶ ማሳካት መቻሉም ተመላክቷል፡፡
ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አንጻርም ከ16 ነጥብ 02 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ እና ወደ ሥራ ገብተው 45 ሺህ 741 ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥሩ ለሚችሉ 310 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡት ሪፖርት የ10 ዓመት ዕቅድን መሰረት ያደረገ እና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ታቅዶ በግማሽ ዓመት ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ ቀዳሚው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት 120 ሺህ 717 የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው÷ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ በኩልም ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሰረተ ልማት ዘርፍ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳደግ 963 የውኃ ተቋማት ቦታ መረጣ እና ግንባታ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ÷ 31 አነስተኛ የውኃ ተቋማት ቦታ መረጣ እና ግንባታ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
ዘመናዊ የመስኖ ልማትን በሚመለከት በ6 ወራት የ15 ነባር ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ስራ 80 ነጥብ 3 ከመቶ እንዲጠናቀቅ መደረጉንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በሰቆጣ የቃል ኪዳን ፕሮግራም 2 ነባር ፕሮጀክቶችን ከነበሩበት 40 በመቶ ወደ 80 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው።
ፍትሕ እና መልካም አስተዳደር ላይም ከወረራ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋጥ የጸጥታ መዋቅሩን አቅም በማሳደግ ሰፊ የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውሰዋል።
በለይኩን ዓለም እና በሙሉጌታ ደሴ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!