የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት የአውሮፓ ህብረት ድጋፉን አዘገየብን ሲሉ ወቀሳ አሰሙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ዩክሬንን ለመረዳት ዘግይተዋል ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቭሎዶሚር ዘነልስኪ ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መደበኛ ስብሰባቸውን በብራስልስ ባካሄዱበት ወቅት ምዕራባውያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ወሳኝ ማዕቀቦችን በሩስያ ላይ ለመጣል ስምምነት አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዘነልሰኪ ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ለመጣል መዘግየቱን ጠቁመው፥ ፈጣን እርምጃዎች ቢወሰዱ ኖሮ “የሩሲያን መጠነ ሰፊ ወረራ” ሊያስቆምልን ይችል ነበር ብለዋል፡፡
“የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ለጣላቸው ማዕቀቦች ምስጋና እናቀርባለን ፤ ነገር ግን ማዕቀቡ የዘገየ ነው” ሲሉም ወቀሳ አቅርበዋል፡፡
ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ፥ ህብረቱ ለዩክሬን የአባልነት ጥያቄ በፍጥነት ውሳኔ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
ቀደም ሲል “የሩሲያ ወታደሮች በማሪዮፖል ግዛት በሚገኘው ቲያትር ቤት ላይ የቦንብ ጥቃት አድረሰዋል ፤ በጥቃቱ ከ300 በላይ ሰዎች ሞተዋል ፤ ንፁሃንንም ዒላማ አድርገዋል” በሚል የዩክሬን ባለስልጣናት በሩሲያ ላይ ክስ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የሩሲያ መከለከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ በበኩላቸው ፥ አገራቸው እያካሄደች ባለው ዘመቻ ንፁሃን ዜጎች ዒላማ አለመሆናቸውን እና የሩስያ ወታደሮች በተቆጣጠሯቸው የዩክሬን ከተሞች የሰብዓዊ ድጋፍ ኮሪደሮች ክፍት መደረጋቸውን በመግለጽ የዩክሬንን ባለስልጣናት ክስ አስተባብለዋል፡፡
የሩስያ -ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ 10 ሚሊየን ዜጎች ከዩክሬን ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መሰደዳቸውን እና በአገር ውስጥ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታውቋል፡፡
ከ10 ሚሊየን ስደተኞች መካከል 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ዩክሬናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ፥ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ ጦርነቱ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው አንፃራዊ ሰላም ወደሚገኝባቸው ወደተለያዩ ዩአገሪቱ ከተሞች መሰደዳቸውን አር ቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!