Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ ፓርቲዎች ላቀረቧቸው አቤቱታዎች ምላሽ ለመስጠት አጣሪ ቡድን አዋቅሮ ምርመራ ማከናወኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎች ላቀረቧቸው አቤቱታዎች ምላሽ ለመስጠት አጣሪ ቡድን አዋቅሮ ሰፊ የምርመራ ሥራ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያየ ነው።

በፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን መነሻ አድረጎ ‘‘ችግር ተፈጥሯል’’ በተባለባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ምርመራ አድርጎ ተገቢው ህጋዊ መፍትሄ እንዲተገበር ማድረጉን በሪፖርት አቅርቧል።

በዚህም በኦነግ እና ኦፌኮ ፓርቲዎች በኩል የተነሱትን አቤቱታዎች በመያዝ ‘‘በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረዋል’’ የተባሉ አባላትን በስፍራው በመገኘት ምርመራዎችን ማከናወኑን የገለጸው ቦርዱ ፥ ህጋዊ አሰራር እንዲተገበር ውሳኔ አስተላልፎ መፍትሄ ማሰጠቱን አንስቷል።

ለዚህም የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የቁም እስረኛ ሆነው መቆየታቸውን በማረጋገጥ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲጠበቅ ቦርዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ መሆኑንና ግለሰቡም በቦርዱ ጽህፈት ቤት ተገኝተው የቦርዱ አመራሮችን ማነጋገራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ቀጣይ በምርመራ ላይ ያሉ የፓርቲዎች አቤቱታዎችን መፍትሄ ለማሰጠት እየሰራ መሆኑን የገለጸው ምርጫ ቦርድ ፥ ከገዥው ፓርቲው በኩል ምላሽ የሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም አሳስቧል።

ቦርዱ ካቀረበው ሪፖርት በመነሳት እየሰራ ላለው ስራም ከፓርቲዎቹ ድጋፍ ተሰጥቶታል።

መንግስት ዘንድሮ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ያደረጉ ፓርቲዎች ተሞክሮ እና ቀጣይ የሚያደርጉ ፓርቲዎች አካሄድ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይቱ ቀጥሏል።

ፓርቲዎችም ለውይይት አጀንዳ ሃሳቦችን እንዲያነሱ እድል ተሰጥቷል።

በዚህም ህጋዊ ፓርቲዎች ላይ እየደረሱ ነው የተባሉ እንግልት እና እስራት፣ እንዲሁም ህጋዊ ፓርቲዎችን ከህግ አግባብ ውጭ ለማክሰም የሚደረጉ ተግባሮች ተጠቅሰው ለውይይት ቀርበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ 50 ሚሊየን ብር ከመንግስት እንደተፈቀደለት አስታውቋል።

መንግስት በጦርነት ምክንያት የወደሙ አካባቢዎችንና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ተግባሮችን በማከናወን ላይ በመሆኑ ቦርዱ የጠየቀውን ያህል ተጨማሪ በጀት ሙሉ በሙሉ ማግኘት እንዳልቻለ ነው የገለጸው።

ከመንግስት የተፈቀደው 50 ሚሊየን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚከፋፈለው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፥ በዋናነት ሴቶችን እና የአካል ጉዳተኞችን የአባል እና አመራር የተገበሩ የሚለው ለገንዘብ ክፍፍሉ ቀዳሚው መስፈርት ይሆናል ተብሏል።

ፓርቲዎችም ይህን ተለትለው ትክክለኛ መረጃ እና በመስፈርቱ የተካተቱ የአባላት ቁጥር እንዲያቀርቡም ተጠይቋል።

በፍሬህይወት ሰፊው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.