የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች የሠላም ሥምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች በወታደራዊ አቅርቦት ላይ ሳይስማሙ ያቆዩትን ጉዳይ እልባት ሰጥተው የሠላም ሥምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ሥምምነቱን የተፈራረሙት በጎረቤት ሱዳን የተካሄደውን ሽምግልና ተከትሎ መሆኑን ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እና ተቀናቃኛቸው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር የተቀናጀ ወታደራዊ ዕዝ ለመመሥረት ነው የተሥማሙት፡፡
የተቀናጀ ወታደራዊ ዕዝ መመሥረታቸው ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ ለቆየው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እልባት ይሰጣል ተብሎም ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡
የኪር የጸጥታ አማካሪ ቱት ጋትሉክ ÷ “ሠላም እንደምንፈልግ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል፤ ሁላችንም ለሠላም እንስራ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በወታደራዊ፣ በፖሊስ እና በብሔራዊ የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ ከሚገኙት 60 ቁልፍ የአመራር ቦታዎች ውስጥ 40 የሚደርሱትን ለመከፋፈል በሚደነግገው የሥምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጁባ ተገኝተዋል።