የገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን በዋግኽምራ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ53 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ53 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌውና የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው በሰቆጣ ከተማ የተደረገው።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዳሉት÷ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ በፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጎጅ ለሆኑ ወገኖች ገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ነው።
እስካሁንም ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ115 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርገናል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅትም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል ከ53 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና አልባሳት ድጋፍ ይዘን መጥተናል ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ሕዝብ ታሪክ ይቅር የማይለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ማድረሱን አንስተዋል።
የዋግ ሕዝብ በኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ታሪክ ለፍትሕና እኩልነት የታገለ፣ ለተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች የማይበገር ጽኑ ሕዝብ ነው ብለዋል።
ይህ ሕዝብ ሲቸገር ድጋፍ ስናደርግ ከፍ ያለ ሐሴት ይሰማናል፤ የሕዝብን ሐብት ለሕዝብ ነው ያበረከትነው ሲሉም አጋርነታቸውን አሳይተዋል።