Fana: At a Speed of Life!

በኢንቨስትመንትና ንግድ አማራጮች ዙሪያ ከእስራኤል ባለሃብቶች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ባራክ ግሩ” ከተሰኘው የንግድ ተቋም ጋር በመተባበር በአገሪቱ የወደብ ከተማ ሃይፋ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና ንግድ ሥራ ዘርፎች ዙሪያ ምክክር አድርጓል፡፡
በውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው በሃይፋ ከተማ የሚገኙ የእስራኤል የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና የንግድ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም የአዳዲስ ኩባንያዎች ባለቤቶችና አመራሮች ተሳትፈዋል።
በወቅቱም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች የሚሰጡ ድጋፎችን በሚመለከት ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ስላሉት የስራ አማራጮች ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ÷ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት፣ ንግድና የቱሪዝም አማራጮችን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለጻው ኢትዮጵያ እና እስራኤል ካላቸው ጠንካራ ትስስር አንጻር የንግድና ኢንስትመንት ትብብሩን ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ መሆኑ ጠቅሰው÷ ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባራክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የመድረኩ አስተባባሪ ኢንጂነር አርኖን ባራክ በበኩላቸው÷ መድረኩ በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ኩባንያዎችን ለማበረታታት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ከኤምባሲው ጋር የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በጋራ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ÷ መሰል የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ከፍ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በእሳቸው ኩባንያ የሚመራ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ያሉትን ኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮች ለማየት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ አላስፈላጊ የሆኑ የቢሮክራሲ ሂደቶችን በመጥቀስ፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሠማራት ያለውን ስጋት ለመቅረፍ በመንግስት ስለሚሰጥ ድጋፍ ሀሳብ አቅርበዋል።
አምባሳደር ረታም መንግስት በኢንቨስተሮች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በመዋቅር፣ በሕግ እና በአስራር ሁኔታዎችን ለማሻሻል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በማስረዳት መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነወ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአገራችን ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ በርካታ የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በተለይ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና አሠራሩን የተሻለ ለማድረግ የወጡትን ሕጎች በማስረጃነት በመጥቀስ ኤምባሲው ችግሮቹን ለመቅረፍ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.