የዋጋ ንረትን በሚያባብሱ ከ103 ሺህ በላይ ህገ-ወጥ አካላት ላይ እርምጃ ተወስዷል- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን በሚያባብሱ 103 ሺህ 901 ህገ-ወጥ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የስምንት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ÷ ባለፉት 8 ወራት የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በተሰጡ መፍትሄዎች ዙሪያ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የአሰራር ሥርዓትን ከማሻሻል አንጻር በንግድ ሥርዓቱ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ብሔራዊ የንግድ እና የጥራት ፖሊሲ እንዲሁም የኤክስፖርት ስትራቴጂ፣ ህጋዊ ስነ-ልክ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ንብረታቸው የወደመባቸው ነጋዴዎችን ለማገዝ የተደረገ ልዩ ድጋፍን፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ንረትን፣ የነዳጅ አቅርቦት ማነስ እና የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪን በሚመለከት ጥያቄ አንስተዋል፡፡
የህገ-ወጥ ደላሎች መብዛት፣ አምራቹ ከተጠቃሚው ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የሚደረገው ጥረት እንዲሁም በመንግሥት ባለስልጣናትና በግሉ ባለሃብቶች መካከል የሚታየውን ያልተገባ ግንኙነትን በተመለከተ ጥያቄዎችን አክለዋል።
በአፋርና አማራ ክልሎች የትህነግ ወራሪ ቡድን በፈፀመው ውድመት የንግድ ፍቃዳቸውን ማሳደስ ያልቻሉትን በመለየት ያለቅጣት አገልግሎት እንዲያገኙናእንዲያድሱ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገልጸዋል፡፡
የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን በሚያባብሱ 103 ሺህ 901 ህገ-ወጥ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የቤት ክራይ የዋጋ ጭማሪ እና የመንግስት ባለስልጣናትን የኑሮ ስታንዳርድ የሚወስን ህግ በሚመለከታቸው አካላት ተዘጋጅቶ መውጣት እንዳለበትም ለምክር ቤቱ አባላት መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!