Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከህዝቡ ጋር በተካሄዱ ውይይቶች የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደ ተግባር መገባቱን አስተዳደሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህዝቡ ጋር ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች ህዝቡ በግልፅነት ያነሳቸውንና በአጭር ጊዜ መመለስ ያለባቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ፡፡
በህዝብ መድረኮች የተነሱት አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች ተለቅመው በእቅድ እንዲመለሱ ለማድረግ የቀሪ 3 ወራት የአስተዳደሩ እቅድ ተከልሶ አመራሩን በማስተባበር ወደ ተግባር ተገብቷል ተብሏል፡፡
ከዋጋ ንረትና ወቅታዊ የኑሮ ውድነት አንፃር ችግሩን ለማቃለል የታቀዱትን ተግባራት መከታተልና ውጤታማ ማድረግ፣ ከስራ እድል ፈጠራና በአጠቃላይ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ ሌብነትን፣ የከተማ ግብርናን ጨምሮ ማህበራዊ ጉዳዮችን የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲያስተባብሯቸው መወሰኑም ተመላክቷል።
ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ የቀረቡ ቅሬታዎችንና አዳዲስ የቤት አማራጮችን ወደ ተግባር በመቀየር ከቤቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ በከተማዋ የኑሮ ውድነት ለከፍተኛ ችግር ተጋላጭ የሆኑትን በልዩ ሁኔታ ማዕድ ከማጋራት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ስርዓት አልበኝነትን ከመቆጣጠርና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ተግባር ተገብቷልም ነው የተባለው፡፡
ከህዝብ ቅሬታ መፍታት ጋር ተያይዞ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ በሳምንት ሁለት ቀናት ረቡዕና አርብ ሙሉ ቀን የትኛውም አመራር ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለህዝቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ አሳልፎ ወደ ተግባር እንደገባም ነው የተገለጸው፡፡
ህዝቡ ያነሳቸውን አንገብጋቢ እና ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ምን እየተሰራ እንደሆነ ለህዝቡ ግልፅነት ለመፍጠር እንጂ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ መደበኛ ስራዎች በታቀደላቸው መሰረት የሚቀጥሉ መሆናቸውንም ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡ ከተማ አስተዳደሩ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ከግብ እንዲደርሱ የተለመደውን ድጋፍ ሊያበረክትና ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊረባረብ እንደሚገባም ጠይቋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.