በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 13 ሺህ 842 የብሬን እና የክላሽ ጥይት ተያዘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መነሻውን ሰሜን ሸዋ ደራ ያደረገው አይሱዚ ተሸከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ጥይት ይዞ ሲንቀሳቀስ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት በጋራ ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር ዋለ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው፥ መነሻውን ሰሜን ሸዋ ደራ ያደረገው አይሱዚ ተሽከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ጥይቶችን ይዞ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር የዋለው መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ፅዮን ሆቴል ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት አካባቢ ነው።
ከህብረተሰቡ የተገኘውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በተደረገ ክትትል ተሽከርካሪው አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ሥር ሲውል÷ በተለያዩ ማዳበሪያዎች የተጫኑ 6 ሸህ 42 የብሬን እና 7 ሺህ 800 የክላሽ በአጠቃላይ 13 ሺህ 842 ጥይት በተሸከርካሪው የውስጥ አካል ተሸሽገው እንደነበረ ፖሊስ አስውቋል፡፡
በዕለቱ በኤግዚቢትነት ከተያዙት ጥይቶች ጋር አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተለያዩ አከባቢዎች ላይ ለሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ህገ ወጦች የሚያካሂዱት የጦር መሳሪያ ዝውውር ዋነኛው መንስኤ መሆኑን በመገንዘብ መላው ሰላም ወዳድ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያጋጥመውና ሲመለከት ለፀጥታ አካላት መረጃ በማቀበልና ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!