ሃይል የማመንጨትሥራውን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታውቋል፡፡
በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ እያየሁ ሁንዴሳ እንደተናገሩት÷ ኃይል የማመንጨት ሥራውን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን በማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ የማዘመን ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓትም በግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የዕለት ተዕለት ስራዎችን፣ የቁጥጥር ሥርዓቱን እና ቴክኒካል የሆኑ የድጋፍ ስራዎችን ዘመናዊ በሆን መልኩ እንዲከናወኑ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ አገር የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ ከጊቤ 3 እስከ ገላን ድረስ የተዘረጉትን መስመሮች እና የጣቢያው ዩኒቶች በማኑዋል ሲፈተሹ እንደነበር ያነሱት ሥራ አስፈፃሚው÷በአሁኑ ሰዓት ስራውን አውቶማቲክ ለማድረግ የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስራውን ለማከናወን 420 ሺህ ዶላር በጀት ተይዞ ዶንግ ፋንግ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት መፈረሙን ነው ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪም በጊቤ 1 እና በበለስ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የስካዳ ማሻሻያ ስራዎችን ለማከናወን የስምምነት ድርድር በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይም የተለያዩ የማዘመን ስራዎች እየተከናወነላቸው ከሚገኙ ማመንጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ በቀጣይ በሌሎች ጣቢያዎች ላይ የማመንጨት ሥራውን ሊያዘምኑ የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን የቴክኒክ ድጋፍ ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዱ ይማም በበኩላቸው÷በጣቢያው ላይ ከዕቅድ ጀምሮ የመለዋወጫ እቃ አቅርቦቱን፣ የዕቃ ግምጃ ቤት አስተዳደርን፣ የመረጃ አያያዝ እና ሪፖርት የማድረግ ስራዎችን በዘመናዊ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በጣቢያው ላይ ትክክለኛ ያልሆነ ድምጽ ሲሰማ ያለውን ችግር በቀላሉ መለየት እንዲቻልና የጣቢያውን የቁጥጥር ስርዓት ማዘምን የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቴክኒካል የሆኑ የድጋፍ ስራዎችን በምስል በተደገፈ መልኩ ከሌላ አካባቢ ከርቀት ሆኖ እንዲከናወኑ ለማድረግ የሚያግዝ የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
በጊቤ 2 ማመንጫ ጣቢያ ላይ እየተከናወነ ያለው የማዘመን ሥራ ከጀርመን መንግስት በድጋፍ የተገኘ ከ677 ሺህ ዩሮ በላይ በጀት ቮይት በተባለ የጀርመን ኩባንያ በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
መጋቢት 2013 ዓ.ም አካባቢ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀ ላይ ሲሆን÷ የኮሚሽኒንግ ስራውን በቅርቡ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡