Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ጀርመን ግንኙነትና ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጀርመን የፓርላማ ልዑክ ቡድንን ተቀብሎ አነጋገረ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ኢትዮጵያና ጀርመን ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከአራት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ብትሆንም በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ጦርነትና በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የድርቅ አደጋ ሳቢያ ሀገሪቱን በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟት ቢሆንም እነዚህን ፈተናዎች ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
መንግስት በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰበት የትግራይ ህዝብ በየብስና በአየር ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ ላይ እንደሚገኝም ለልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም የሚታዩ የልዩነት ሀሳቦችን ሁሉም አካላት በማሳተፍ በውይይትና በምክክር ለመፍታት እንዲቻል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
አክለውም ፥ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ “ግድቡ የኔ ነው” በሚል መፈክር በራሷ ህዝቦች መዋጮ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ፣ ግድቡም የሌሎችን ሀገሮች ጥቅም የማይጎዳ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነት በቴክኖሎጂ እየደገፈች እንደምትገኝ ጠቁመው ፥ ወደፊትም በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በቴክኒክ እንዲሁም ተቋማትን መልሶ በመገንባት ረገድ ድጋፏን እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
የጀርመን ፓርላማ አባል የሆኑት ሮድሪች ኪይስዌተር በበኩላቸው ፥ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ጀርመን ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ በተለይም በቴሌኮም ዘርፍ እየደገፈች መሆኑን አስታውሰው ፥ በቀጣይም በትምህርት፣ በልምድ ልውውጥ እና በቴክኒክ ረገድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.