በአማራ እና አፋር ክልሎች እርዳታን ለማድረስ የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ተሳትፎ መሻሻል አሳይቷል – ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ተሳትፎ መሻሻል ማሳየቱን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ሲስተዋል የነበረው እርዳታ እቀባ አሁን ላይ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአፋርና አማራ ክልሎች ለሚገኙ ተረጂዎች የሚደረገው ድጋፍ በቂ የማይባልና የበለጠ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
መንግስት ለትግራይ ክልል የአብዓላ ኮሪደርን በመጠቀም በየብስ እርዳታ እያቀረበ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ከሁለት ሳምንታት በፊት የመጀመሪያው እርዳታ መላኩን እና ሁለተኛውን ለመላክ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከየብስ ባለፈ በአየር ትራንስፖርት ወሳኝ የሆኑ እርዳታዎች እየተላኩ መሆናቸውን ገልጸው÷መድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ ለህፃናትና እናቶች የሚውሉ አልሚ ምግቦች እየተጓጓዙ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ማክሰኞና ሀሙስ የነበረውን በረራ በአሁኑ ወቅት የአጋር አካላት አቅም እስከፈቀደ ድረስ በረራ ክፍት መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህም መሰረት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበርን ጨምሮ ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች እርዳታ እያጓጓዙ ነው ብለዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!