በዋግ ኽምራ በህውሃት ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለተዘረፉ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩ.ኤስ.ኤይድ ትራንስፎርም ፕራይሜሪ ሄልዝ ኬር ፓዝ ፋይንደር በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለተዘረፉ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ የዩ.ኤስ. ኤይድ ትራንስፎርም ፕራይሜሪ ሄልዝ ኬር ፕሮጀክት ሃላፊ እና ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ አስናቀ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የእናቶችና ህፃናት ጤና ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም÷ በጦርነቱ ምክንያት በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ለወደሙ የጤና ተቋማት ቀደም ሲል 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለ20 ጤና ጣቢያዎችና ለ3 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚውል 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ከድጋፉ ውስጥም የእናቶች ማዋለጃ፣ የህሙማን መተኛ፣ የቤተ ሙከራና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የመኝታ ፍራሽ፣ የማብሰያ ቁሳቁስ፣ አንሶላ፣ ብርድ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፈ ተደርጓል።
በቀጣይም በአማራ ክልል የወደሙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለመመለስና ለማጠናከር 123 ሚሊየን ብር በመመደብ የህክምና ቁሳቁስ ለመደገፍ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የሽብር ቡድኑ በብሄረሰብ አስተዳደሩ በፈፀመው ወረራ ምክንያት ከ400 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የጤና ተቋማት ውድመት ማድረሱ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ፓዝ ፋይንደርን ጨምሮ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያደረጉት ድጋፍ ከወደመው ንብረት አንፃር 10 በመቶውን ያህል መሆኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡