የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የ60 ቀናት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።
ከንቲባዋ ከዚህ በፊት በርካታ ሰው ተኮር የሆኑ ተግባራት በክፍለ ከተማው በፍጥነት ተገንብተው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም እነዚህን ግንባታዎች፣ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች፣ የከተማ ማስዋብና የከተማ ግብርና ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም አብዛኞቹ ስራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም ችግሮች ካሉ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የሚፈቱበትን አግባብ ለማመቻቸት ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክትትሉም በየወቅቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡