የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በደቡብ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የአትክልትና ፍራፍሬ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በቡታጅራ ማዕከል ሲሰለጥኑ የነበሩት የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በሞዴል አርሶ አደሮች እየለማ ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።
የዞኑ አርሶ አደሮች በተለይ አቮካዶ በማልማት ወደ ውጭ እየላኩ መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል።
የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ፥ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየለማ ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ በአጭር ጊዜ ከድኅነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ፥ በሞዴል አርሶ አደሮች እየተካሔደ ያለው የግብርና ሥራ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል።
በየደረጃው እየተካሔደ ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
በጉብኝቱ የተሳተፉ አመራሮች እንዳሉት፥ በክልሉ በልዩ ልዩ የግብርና ልማት ሥራ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያካሔዱት ያለው የልማት ሥራ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ያግዛል።
በሞዴል አርሶ አደሮች የተጀመረው ልማት ወደ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ መሥራት እንደሚገባ መጠቆማቸውን ያመላከተው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ነው።
በክልሉ በአራት ማዕከላት ሰሞኑን በሥልጠና ላይ የነበሩ የብልጽግና ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች በቡታጅራ፣ በሆናዕና፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዶ ከተማና አጎራባች ዞኖች በሞዴል አርሶ አደሮች የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተሞክሮ ነው የተመለከቱት።