በካሊፎርኒያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት አንድ ሰው በኮሮና ቫይረስ መሞቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።
በግዛቷ የ71 ዓመት አዛውንት በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈት ተዳርገዋል፤ አዛውንቱ ባለፈው ወር መነሻዋን ሳንፍራንሲስኮ ባደረገችው መርከብ ሳይሳፈሩ እንዳልቀረ ተገልጿል።
የአዛውንቱ ህልፈት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በአሜሪካ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 11 አድርሶታል፤ 150 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተጠቅተዋል ነው የተባለው።
የአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርና የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ዋሽንግተን እና ፍሎሪዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል።
ከኋይት ሃውስ የወጡ መረጃዎች ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመላው አሜሪካ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ያመላክታል።
ለኮሮና ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመውን ቡድን የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስ ማንኛውም አሜሪካዊ በህክምና ባለሙያ ከታዘዘ ግዴታ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ዓለም ላይ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ከ92 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መጠቃታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision