መምህራን ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ የሰላም ግንባታን ለማሳካት የማይተካ ሚና አላቸው- ሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ የሰላም ግንባታን ለማሳካት መምህራን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር ሲያካሂድ የቆየው ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
በመድረኩ ለሀገራዊ ዘላቂ ሰላም ግንባታ የትምህርት ማህበረሰብ ሚና፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰላም ትምህርት አካቶ እና ያለ ሰላም ትምህርት፥ ያለ ትምህርት ሰላም እንዲሁም በግል ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራት ለዘላቂ ሰላም ያለው አንድምታ በሚሉ ርዕሶች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ተሳታፊዎች ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ገልጸው÷ ሰላም ከሌለ የመማር ማስተማር ሂደትም ሊኖር እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል፡፡
ስለሆነም በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁላችንም በየተሰማራንበት አካባቢ የበኩላችንን ለመወጣት እንሰራለን ማለታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ ወንድወሰን መኮንን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ትውልዱን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ የሰላም ግንባታ ለማሳካት መምህራን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ስለሆነም የዘላቂ ሰላም ሂደትን እውን ለማድረግ የሰለጠነ እና በባህሉ የሚኮራ ማህበረሰብ ለመገንባት መምህራን ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡