Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር ከተማ ሰዎችን በማገት የተጠረጠሩ 36 ግለሰቦች በቁጥጥ ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ሰዎችን በማገት የተጠረጠሩ 36 ግለሰቦች በቁጥጥ ስር መዋላቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በሕግ ማስከበር እንቅስቃሴው ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሰጡት መግለጫ÷ በከተማዋ የእገታ፣ የመሬት ወረራ እና የጥይት ተኩስ መበራከት ለከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
የከተማዋን ነዋሪዎች ጥያቄ ለመመለስም የሕግ ማስከበር ሥራ መጀመሩን ገልጸው÷ ከፍረጃ በፀዳ ሁኔታ የሕግ ማስከበር ስራዎች መከናወናቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሰዎችን በማገት ወንጀል የተጠረጠሩ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሕግ ማስከበሩ ጋር በተያያዘ 10 የመንግስት ቤቶችን በኃይል ሰብረው የገቡ ግለሰቦች ቤቱን አስረክበው እንዲወጡ መደረጉን÷ በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡ 103 ቤቶች መፍረሳቸውን እንዲሁም 102 በሕገ ወጥ መንገድ ታጥረው የነበሩ የመንግስት ቦታዎችን ማፍረስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡ 106 ሸዶችና ኮንቲነሮችን ማስነሳት መቻሉን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
የሕግ ማስከበር ሥራው ፋኖን ለመያዝ እና ትጥቅ ለማስፈታት ነው እየተባለ የሚይናፈሰው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ያወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው÷ ከእውነተኛ ፋኖዎች ጋር በጋራ በሕግ ማስከበር ሥራው ተስማምተን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም አሁን ያለውን ሁኔታ በመረዳት ለፀጥታ ኃይሉ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በክብረወሰን ኑሩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.