በካቡል በተፈጸመ ጥቃት 27 ሰዎች ተገደሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ የ27 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው በ1995 በታሊባኖች የተገደለው የሀዝራ ጎሳ መሪ አብዱል አሊ ማዛሪ መታሰቢያ በዓል ላይ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ጥቃት ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የአፍጋኒስታኑ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ አብዱላሂ አብዱ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ጉዳት ሳያጋጥማቸው አምልጠዋል ነው የተባለው፡፡
ጥቃቱ አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ስምምነት ላይ ከደረሰች ወዲህ ትልቁ ጥቃት ነው ተብሏል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ ታሊባን በበኩሉ በጥቃቱ እጁ እንደሌለበት አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱንና በስፍራው ሮኬት ማረፉን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፊ ጋኒ፥ ጥቃቱን በሰው ልጆች እና በአፍጋኒስታን ብሄራዊ አንድነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ብለውታል፡፡
ባለፈው ዓመት በተከበረው ተመሳሳይ መታሰቢያ በዓል ላይ መሰል ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ምንጭ፦ ሬውተርስ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision