የዋቸሞ እና ሚዜን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዱራሜ ካምፓስ እና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር ያሰለጠኗቸውን ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አስመርቀዋል፡፡
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በዱራሜ ካምፓስ በተለያየ የሙያ መስክ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 273 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው፡፡
ካምፓሱ በ5ኛ ዙር ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል÷ 13ቱ በሁለተኛ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁ ናቸው፡፡
የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚንስትር ዴኤታ እና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ÷ በትምህርት ዘርፉ አገር ወዳድ፣ ታታሪና ታማኝ ዜጋ በተከታታይ ለማፍራት ባለመቻሉ አሁን አገር ላይ እየገጠመ ያለው በስሜት የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዲበራከቱ ሆነዋል ብለዋል፡፡
ከጊዜው ቴክኖሎጂ ጋር በመራመድ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው በግብርና ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የጀመራቸውን ክንውኖች የበለጠ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይም የቡና፣ አቮካዶ፣ ድንች፣ ቦቆሎና ጤፍ ምርጥ ዘርን በማላመድ የሀዲያና ከምባታ ጠባሮ ዞን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የወተት ላሞችን እያዳቀለ መሆኑን ጠቁመው÷ በተለይም የከተማ ግብርናን በአካባቢው እያላመደ መሆኑንም ገልጿል፡፡
በ2017 ዓ.ም 10 ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ የማድረግና በቱሪዝም በተለይም በሜድስን ቱሪዝም ልዩ መዳረሻ ለመሆን እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በትላንትናው ዕለትም በዋናው ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 1ሺህ 510 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን ለ14ኛ ጊዜ አስመርቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ÷ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ቀልጣፋ ለማድረግ የአይ ሲ ቲ መሠረተ ልማትን የማዘመን ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጥናትና ምርምር ዘርፍም ለሀገር በቀል ዕውቀት ትኩረት መሠጠቱንና ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማጣመር መስራት የሚያስችል ተቋም መመስረቱን ገልጸዋል፡፡
በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ባደረጉት ንግግር÷ ተመራቂ ተማሪዎች “ተመርቃችሁ ስትወጡ ሁሉ ነገር አለቀ” ብላችሁ ሳትቀመጡ ለሌላ ብርቱ ትግል ራሳችሁን ማዘጋጀት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡
በጌታቸው ሙለታ እና አደም አሊ
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!