Fana: At a Speed of Life!

በደሴ በተከሰተ ፍንዳታ በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ በተለምዶ ሳላይሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተከሰተ ፍንዳታ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በደሴ ከተማ የ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አለባቸው መለሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ ዛሬ 5 ሰዓት ከ30 ላይ ሳላይሽ በግ ተራ አካባቢ የቆራሌ ዕቃ በሚራገፍበት ሰዓት ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ፈንድቶ በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

በፍንዳታው በግ ሲገዙ የነበሩ ሰዎችና የቀን ሠራተኞች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን÷ ተጎጂዎችም ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የፖሊስ መረጃ እንደሚያመላክተው÷ እስከ አሁን ድረስ ከ36 በላይ ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን÷ ከ15 በላይ በቦታው ለሽያጭ የቀረቡ በጎች ሞተዋል።

የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ከበደ በሽር በበኩላቸው÷ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በፍንዳታው ምክንያት ሰው እንደሞተ ተደርጎ የሚወራው መሰረተ ቢስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን ጠቁመው÷ የተለየ መረጃ ሲኖረውም ያሳውቃል ብለዋል፡፡

ፖሊስ የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ጥብቅ ምርመራ እያካሄደ መሆኑም ተገልጿል።

በከድር መሀመድ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.