አብላጫው አሜሪካዊ ጆ ባይደን በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የለባቸውም ብሎ እንደሚያምን ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አብላጫው አሜሪካዊ ጆ ባይደን በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የለባቸውም ብሎ እንደሚያምን የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት አመለከተ።
ያሁ ኒውስ በቅርቡ ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት መሰረት፥ ድምፅ ሰጪ አሜሪካውያን መካከል በፈረንጆቹ 2024 በሚካሄደው ምርጫ ፕሬዚዳንት ባይደን በድጋሚ መወዳደርን የደገፉት 18 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ፥ 64 ከመቶዎቹ ደግሞ ሊወዳደሩ አይግባም ብለው ያምናሉ።
ውጤቱ በስልጣን እያሉ ዝቅተኛ የህዝብ ቅቡልነት ካገኙ የሀገሪቱ መሪዎች መካከል ባይደንን አንዱ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው።
የህዝብ አስተያየቱ ውጤት እንደሚጠቁመው ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ፕሬዚዳንቱ ያላቸው የህዝብ ቅቡልነት እያሸቆለቆለ መጥቶ 41 በመቶ ዴሞክራቶች በቀጣዩ ምርጫ ባይደንን እጩ ሆነው መመልከት እንደማይሹ የገለፁ ሲሆን፥ 35 በመቶዎቹ ዴሞክራቶች ግን በድጋሚ መወዳደራቸውን ደግፈዋል።
በባይደን ቦታ ማን ይወዳደር በሚለው ሃሳብ ዙሪያም ዴሞክራቶች ተከፋፍለዋል።
19 በመቶ የሚሆኑት ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስን ሲጠቁሙ፥ 20 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሌላ ሰው ቢወዳደር ያሉ ናቸው፡፡
30 በመቶ የሚሆኑት እስካሁን እንዳልወሰኑ ሲገለፅ፥ 4 በመቶ የሚሆኑት ግን በምርጫው ድምፅ እንደማይሰጡ ነው የገለፁት።
ምንም እንኳን ባይደን በሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ቢገልፁም ፥ ጥናቱ አብዛኛዎቹ ዴሞክራቶች በ79 ዓመቱ ፕሬዚዳንት እጩነት ላይ እርግጠኛ ያልሆኑ ይመስላሉ ሲል አር ቲ ዘግቧል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!