በተለያዩ ከተሞች በ104 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶችና ቅርንጫፎች ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶችና ቅርንጫፎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ተቋማቱ የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው የእውቅና ፈቃድ ባልተሰጠባቸው ካምፓሶች፣ ቅርንጫፎች እና የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብለው ሲያስተምሩ፣ የእውቅና ፈቃድ እድሳት ባልተሰጠባቸው የትምህርት መስኮች መዝገበው ሲያስተምሩ በመገኘታቸው ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተቋማቱ ባልተፈቀደበት የትምህርት አሰጣጥ ክፍለ ጊዜ ማለትም በሳምንቱ የመጨረሻ ሁለት ቀናት ቅዳሜና እሁድ እና በማታ ክፍለ ጊዜ በማስተማራቸው፣ ፈቃድ ባገኙበት ካምፓስ ላይ አለመገኘት፤ እንዲሁም በእውቅና ፈቃድ እና በእውቅና ፈቃድ እድሳት ወቅት ተሟልተው የነበሩ ግብዓቶችን አጓድለው መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡
ተቋማቱ የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ በፕሮግራም፣ በካምፓስና በተቋማት ደረጃ የእውቅና ፈቃዳቸው ተሰርዞ ሙሉ ለሙሉ የተዘጉ እንዳሉም ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
በ2014 ዓ.ም ብቻ በአዲስ አበባ 106፣ በክልል ከተሞች በ1ኛ ዙር 95 እና በ2ኛ ዙር 104 በድምሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመመሪያ ጥሰት በተገኘባቸው 305 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ካምፓሶች እና ቅርንጫፎች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ለሕዝብ ይፋ መደረጉንም አስታውሷል፡፡
ተጨማሪ የእርምት እርምጃዎች በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚደረጉም ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡