የብሪታንያዋ የጤና ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታንያዋ የጤና ሚኒስትር ናዲን ዶሪስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።
የወግ አጥባቂው የፓርላማ አባል የሆኑት ሚኒስትሯ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ አሁን ላይ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እንዲቆዩ ተደርጓል ነው የተባለው።
ዶሪስ በቫይረሱ የተጠቁ የመጀመሪያዋ የፓርላማ አባል ሲሆኑ፥ አሁን ላይ በሃገሪቱ 382 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ ስድስት ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል።
የ62 አመቷ ሚኒስትር ላይ ምልክቱ ካለፈው ሳምንት ሃሙስ ጀምሮ ሳይታይባቸው እንዳልቀረም ተገልጿል።
ይሁን እንጅ በእነዚህ ቀናቶች በተካሄዱ የካቢኔ ስብሰባዎች ላይ ከምን ያህል ሰዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አልተገኙም።
ይህን ተከትሎም የሃገሪቱ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት ሚኒስትሮችና የፓርላማ አባላት ላይ ምርመራ ለማድረግ ስለማሰቡ ገልጿል።
የእንግሊዝ ባንክም ኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚሰጠው የወለድ ምጣኔ ላይ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህም ባንኩ ከዚህ በፊት የነበረውን የወለድ ምጣኔ ከ0 ነጥብ 75 ወደ 0 ነጥብ 25 ዝቅ ማድረጉን ገልጿል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision