አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እየተደረገ ባለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መንግስት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ማይክ ሐመር በበኩላቸው÷ አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመረውን የሰላም ውይይት ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ማረጋገጣቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ልዩ መልዕክተኛው÷አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰደ ላለው አበረታች ጥረት እውቅና እንደምትሰጥም አንስተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!