የኢትዮጵያ እና ግሪክን ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ መስራት ይገባል – የግሪክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሀገራቱ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒኮስ ዴንዲያስ ገለጹ፡፡
በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ከግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒኮስ ዴንዲያስ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ ሁለቱም ወገኖች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ግንኙነቱን ለማጠናከር በትብብር ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳለ ገልፀው ፥ ይህንን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በጋራ ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ እንደምታልፍ ሙሉ እምነት አለኝ ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ለሰላምና ለልማት በሚያስፈልጉ ድጋፎች ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ቃል መግባታቸውን በጣሊያን ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ደሚቱ ፥ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም መንግስት ለልማት፣ ለሰላም እና ከጋራ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት ፤ ስለ ሰብዓዊ እርዳታ ፤ አካታች ብሄራዊ ምክክር ለማድረግ ስለተከናወኑ ተግባራት እና መሰል ጉዳዮች ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!