የብልጽግና ፓርቲ አባላት በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መላው የብልጽግና ፓርቲ አባላት ኢትዮጵያን አረንረጓዴ የማልበስ አላማ ባለው የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ጥሪ አቀረቡ።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት አመራሮች እና ሠራተኞች በአዲስ አበባ የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ችግኝ ተክለዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ስትራቴጂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ብልፅግና ፓርቲ በልዩ ትኩረት የሚፈፅመው ተልዕኮ ነው ብለዋል።
ከ12 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ለመርሐ ግብሩ ትግበራ ትልቅ አቅም በመሆናቸው÷ በየአካባቢያቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልል እና ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተግባሩን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲያስተባብሩ ጠይቀዋል።
አዳዲስ ችግኞችን ከመትከል በተጨማሪ የተተከሉትን በአግባቡ የመንከባከቡ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
አቶ አደም በጊዜያዊነት በሚያጋጥሙ ችግሮች ሳንሰናከል ችግኞችን እየተከልን ችግሮችን እየነቀልን ወደ ብልጽግና መገስገሳችን ይቀጥላል ብለዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ሲሆን÷ መርሐ ግብሩ ጎረቤት ሀገራትንም ባሳተፈ መልኩ እንዲሰፋ እየተሰራ መሆኑን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!