ለቀናት ሲካሄድ የነበረው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ የፓርቲው ፅህፈት ቤት ገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ገለፁ።
የስልጠናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ አቶ ፍቃዱ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም 10 ሺህ የሚሆኑ መካከለኛ አመራሮች የለውጡ ትሩፋቶች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም የፓርቲው ፕሮግራምን አስመልክቶ መሰልጠናቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን የብልፅግና ምሳሌ ማድረግን ውጥኑ ያደረገው የ10 አመቱ እቅድም የውይይቱ አካል እንደነበር ገልፀዋል።
ወቅታዊ የህዝብ ጥያቄና ፍላጎቶችም የተቃኙ እንደነበሩ በማንሳት በዚህም በአመራሩ ዘንድ የጠራ ግንዛቤ እና የተግባርና የአመለካከት አንድነት መፍጠር የሚያስችል ነበር ብለዋል።
አመራሮቹ ወደየመጡበት ሲመለሱም የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ግጭቶችን የመፍታትና፣ የጥላቻ ፓለቲካን የማስወገድ፣ በዋናነትም የህዝቡን ጥያቄ የመመለስ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
ህዝቡም ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ መሳካት ከአመራሩ ጋር በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት አቶ ፈቃዱ።
ከስልጠናው ጎን ለጎንም ግምገማ መካሄዱን የገለፁት አቶ ፍቃዱ ለሰባት ቀናት የሚካሄደውና 150 ሺህ ጀማሪ አመራሮችን ለሚያሳትፈው ስልጠና ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ሀብታሙ ተክለስላሴ