የሩሲያ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት የባለ ብዙ አቅጣጫ አጋርነት ማሳያ ሞዴል ነው – አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሩ ኮሪብኮ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት የባለ ብዙ አቅጣጫ አጋርነት ማሳያ ሞዴል መሆኑን መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገው አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሩ ኮሪብኮ ገለጸ።
አንድሩ ኮሪኮብ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአፍሪካ የመጨረሻ ጉብኝታቸው የአፍሪካ ኅብረት መገኛ በሆነችው አዲስ አበባ መገኘታቸውን ተከትሎ ባወጣው ፅሁፍ፥ የላቭሮቭ ጉብኝት ሩሲያ ከመላው የአፍሪካ ሀገራ ጋር ያላትን የጋራ እና ሁለገብ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ፍላጎት ያሳየ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
አንድሩ፥ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ብቻ ሳትሆን የፀረ-ኢምፔሪያሊዝም እና የፓን አፍሪካኒዝም ታሪካዊ መገኛ በመሆኗ የአህጉሩ መንፈሳዊ መዲና ናት ብለው በርካቶች እንደሚያምኑም በጽሑፉ አውስቷል፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት ከ19 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ የቀጠለ መሆኑንም አትቷል፡፡
ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ሩሲያ እና ኢትዮጵያ እውነተኛ አጋር ሀገራት ሆነው እንደቀጠሉና በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንደሚተባበሩም ነው ያመላከተው፡፡
ለአብነትም ፥ በህወሓት ቀስቃሽነት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት እና ምዕራባውያን ሤራዎች ሲጎነጎኑባት እና ተጽዕኖ ሲደርስባት እንደነበር አስታውሶ በወቅቱ ሩሲያ ኢትዮጵያ ላይ ሊወሰዱ የታሰቡትን እርምጃዎች ባለመደገፍ በመርኅ ላይ የተመሰረተ ገለልተኝነቷን ማሳየቷን እና ለምዕራባውያኑ ድጋፍ መንፈጓን ፅፏል፡፡
በአሁኑ የሰርጌይ ላቭሮቭ ጉብኝትም ኢትዮጵያ ጦርነቱ ካሳረፈባት ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንድታገግም ለመርዳት ቃል መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡
ይህም እንደ ቻይና እና ሕንድ ያሉ የተሻለ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት እንደ ምዕራብ አፍሪካ ያሉ ሌሎች በጦርነት የተጎዱ የአፍሪካ አጋሮቻቸውን መልሶ ለመገንባት ምሳሌ እንደሚሆናቸው አመላክቷል፡፡
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ለቀሪው ዓለም በተለይም ለአፍሪካ ሀገራት እንዴት ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት እንደሚቻል በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋልም ነው ያለው አንድሪው።
አንድሩ ኮሪብኮ በጽሑፉ ማጠቃለያ ላቭሮቭ ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ የሩሲያ አና የኢትዮጵያ መጻዒ ግንኙነት ጠንካራ እንደሚሆን ከወዲሁ የጠቆመ ነው ብሏል።