በመደጋገፍ ከተሠራ የማይታለፍ ችግርና ፈተና አይኖርም – ዶ/ር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመደጋገፍና በመተባበር ከተሠራ የማይታለፍ ችግርና ፈተና አይኖርም ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ቴና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በክረምቱ የሚከናወኑ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳትና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አስጀምረዋል፡፡
ዶክተር ሊያ÷ በመንግሥትም ሆነ በግል ተባብሮ በመሥራት የአቅመ ደካሞችን ሕይወት ለመለወጥ ተግቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመደጋገፍና በመተባበር በአንድነት ከተሠራ የማይታለፍ ችግርና ፈተና አይኖርምም ነው ያሉት።
ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመተባበር በጋምቤላ ከተማ የአምስት፣ በአዲስ አበባ ደግሞ የ12 የአቅመ ደካማ ቤቶችን የማሳደስ ሥራ ማስጀመሩን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በጋምቤላ ከተማ ለ400 የአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው የትምህርት ቁሳቁሱ ድጋፍ ለአዲስ አበባ ከተማም መሰባሰቡን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ለማገዝ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የተተከሉትን ጨምሮ ከ62 ሺህ በላይ ችግኝ መትከላቸውን ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በመተባበር በሚቀጥለው ወር ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ለአቅመ ደካሞች የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ዶክተር ሊያ አንስተዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ÷ ጤና ሚኒስቴር የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያልደረሳቸውን አቅመ ደካሞች በመደገፍ ረገድ ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
ሚኒስቴሩ ለአቅመ ደካሞች ሊሰጥ ላቀደው የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ስኬታማነት የክልሉ መንግሥት ድጋፍና ትብብሩ ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-