Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲያስችሉ ይደረጋል -አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያሉ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲያስችሉ የማድረግ ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ፡፡

በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ መንደር 13 ቀበሌ፥ በ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችሉ ትምህርት ቤቶች ሊሆኑ ይገባል።

ለዚህም የክልሉ መንግሥት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

አርሶ አደሩም በማሰልጠኛ ተቋሙ የለሙና ውጤታማ የሰብል ዝርያዎችን በራሱ መሬት ላይ በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዉጤታማ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ማሰልጠኛ ማዕከሉን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ ኡሞድ አስታውቀዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው÷ አርሶ አደሩ ከሚያየው እንዲማርና የተሻለውን ወደራሱ ማሳ ወስዶ ተግባራዊ እንደዲያደርግ ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ማሰልጠኛ ማዕከሉን ገንብቶ ለማስረከብ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር እንደፈጀ ጠቁመው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.