ወደ ሥራ ሳይገቡ የቆዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ጥቅም ላይ ማዋል የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሆን ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሥራ ሳይገቡ የቆዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ጥቅም ላይ ማዋል የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሆን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ እና የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
በውይይቱ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እንደገለፁት፥ ድርቅ ላጠቃቸው ቆላማ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የእንስሳት መኖዎችን አልምቶ ለማቅረብ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በዚህም ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የእንስሳት መኖ አልምቶ በድርቁ ለተጎዱት ወገኖች ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርቅ ባጠቃቸው ቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚሆን ከ19 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የውሃ እና መኖ አቅርቦት መደረጉንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ÷ ለመስኖ ግንባታ መጓተት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች በስፋት እና በተጠናከረ መንገድ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቀላል በሆኑ እና ሊፈቱ በሚቻሉ ችግሮች የተነሳ ወደ ሥራ ሳይገቡ የቆዩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ጥቅም ላይ ማዋል የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በዳንኤል አማረ