የአስተዳደር ወሰኑ መካለል ለሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ጥሩ መሰረት የጣለ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስተዳደር ወሰኑ መካለል ለሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ለሚሰራው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ጥሩ መሰረት የጣለ መሆኑን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
የአስተዳደር ወሰን መካለል የሕዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር፣ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ የወሰን ማካለል ሂደት ተግባራዊ ሲደረግ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር እንደመነሻ መወሰዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት÷ የአስተዳደር ወሰን መካለሉ ከአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ባሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ድል ነው።
እስከ አሁን ይህ ወሰን ባለመኖሩ የሁለቱም ነዋሪ ሕዝቦች ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን አስታውሰው÷ አሁን ትልቅ ስኬት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ከሕዝብ ይልቅ የመሬትን ሃብት ብቻ በማሰብ ያለፉት ሥርዓቶች በሁለቱም ወገን ባሉ ነዋሪዎች ላይ ዘርፈ- ብዙ ጉዳቶች ሲያደርሱ መቆየታቸውንም ነው ያወሱት፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሥልጣን የያዘው መንግሥት ግን ለሕዝቡ የልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሾችን በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የአስተዳደር ወሰን ጉዳይም የሕዝቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ ቆይቶ ምላሽ ማግኘቱን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ በሁለቱም ነዋሪዎች ላይ በደል ማድረስም ሆነ የዘርፋ ተግባር መፈጸም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
ውሳኔው ለሕዝቡ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ጠቁመው÷ በቀጣይ ለሚሠሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ታላቅ ሽግግር ይሆናል ብለዋል።
ውሳኔውን መሬት ለማስያዝና ለነዋሪው የሚሰጠው አገልግሎት እንዳይቆራረጥ የጋራ ጽሕፈት ቤት እንደሚቋቋምም ጠቁመዋል።
ሕዝቡን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰርም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ያረጋገጡት፡፡